የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአትላንታ በሚያከናውነው ጨዋታ ምትክ ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ በማምራት ባሳለፍነው ረቡዕ ከጉያና ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ 2-0 ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በቀጣይ ቅዳሜ ከአትላንታ ሮቨርስ ጋር ሁለተኛ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ቢይዝም አዘጋጁ ተቋም የጨዋታው ትኬት በበቂ ሁኔታ እንዳልተሸጠ በመግለፅ ጨዋታው እንዲሰረዝ መጠየቀን ተከትሎ በአትላንታው ጨዋታ ምትክ ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ እንዲዘጋጅ ተደርጓል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አትላንታ የማይጓዝ ሲሆን በምትኩ በዋሺንግተን ዲሲ ቆይታ በማድረግ የተለያዩ ጨዋታዎች ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በዚህም መሰረት በመጪው ቅዳሜ ሐምሌ 29 ከሎዶን ዩናይትድ ጋር በሴግራ ፊልድ የሚጫወት ይሆናል። ሎዶን ዩናይትድ መቀመጫውን በሊዝበርግ ቨርጂንያ ያደረገና በUCL Championsip የሚካፍል ቡድን ሲሆን ብሔራዊ ቡድናችን ከጉያና ጋር ያደረገው ጨዋታ የተካሄደበት ሴግራ ፊልድ ባለንብረት ነው።
ከቅዳሜው የወዳጅነት ጨዋታ በመቀጠል ብሔራዊ ቡድናችን ከዲሲ ዩናይትድ ክለብ ጋር ጨዋታ እንዲያደርግ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን ክለቡ ይህን ጨዋታ እንዲያደርግ በአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (US SOCCER) ፍቃድ ካገኘ የሚካሄድ ይሆናል። ለዚህም ጨዋታ መሳካት የዲሲ ዩናይትድ ክለብ ባለድርሻ የሆኑት ኢዮብ ማሞ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን ለዚህ እና በአጠቃላይ ቡድናችን በአሜሪካ ቆይታው ላይ እያደረጉት ለሚገኘው ትብብር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ልባዊ ምስጋውን ያቀርባል።
ኢእፌ